Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ አስተዳደር የመስቀል ደመራ በዓል ከምጊዜውም በላይ በደመቀና በላቀ ሁኔታ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መጠናቀቁን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራ በዓል በከተማዋ ከ2 ሺህ 200 ቦታዎች በላይ ከምንጊዜውም በላይ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ትውፊቶቹንና ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን ገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ የመስቀል በዓልን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም÷ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ በዓሉ የጋራ በዓላችንና ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ ነው በማለት በዓሉ ከሃይማኖታዊ ገፅታው ባሻገር የኢትዮጵያ መልካም ገፅታ መገለጫና የኢትዮጵያ ሰላም ወዳድነት ማሳያ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ብሏል፡፡

ነዋሪው÷ በአብሮነት ለደመራውና ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማዘጋጀት አካባቢውን በማስዋብ ድንቅ ኢትዮጵያዊ እሴት ጎልቶ እንዲወጣና ከተማችን የኅብረብሔራዊነትና የመተባበር ተምሳሌት መሆኗን አሳይቷል ብሏል አስተዳደሩ በመግለጫው፡፡

እንዲሁም የፀረ ሰላም ኃይሎች የበዓሉን ድባብ ለማጥፋት የአገራችንን ገፅታ ለማበላሸት የሞት የሽረት ትንቅንቅ ያደረጉበትና አዲስ አበባን የሽብር ማዕከል ለማድረግ ብዙ ሃብት አፍስሰው የሰው ኃይል አሰማርተው ከበዓሉ ቀደም ብለው ሲዘጋጁበት የነበረው የሽብር እቅዳቸው በሕዝቡና በፀጥታ ኃይሉ ትብብር ምኞታቸው ቅዠት ሆኖ መቅረቱን ገልጿል መግለጫው፡፡

በዚህም ፀረ ሰላም ኃይሎችን አጋልጦ በመስጠት በርካታ ተላላኪዎችና ለሽብር ድርጊት ሊውሉ የተዘጋጁ መሳርያዎች ጭምር በየአካባቢው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የልዩነትና የመከፋፈል አጀንዳዎችን በማስወገድ በንቃትና በትጋት በአንድነት ተናበንና ተዋኅደን ዘላቂ ሰላማችንን ልናረጋግጥ ብሎም እነዚህን ኃይሎች እስከ መጨረሻው ተስፋ ልናስቆርጥ ይገባል ብሏል።

ፀረ ሰላም ኃይሎች ምንም ቢተባበሩና የፈለገውን ያህል ቢዘጋጁ ከሕዝባችንና ከፀጥታ ኃይላችን ዐይንና ጆሮ የማያመልጡና ለዘላቂ ሰላማችን ስጋት ሊሆኑ እንደማይችሉ በጉልህ ያረጋገጥንበት በዓል ነው ብሏል ከተማ አስተዳደሩ፡፡

በመስቀል ዐደባባይ እና በየአካባቢው የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅና ሰላማዊ ሁኔታ ሃይማኖታዊ እሴቱንና ስርዓቱን ከፍ አድርጎ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ከተማ አስተዳደሩ አመስግኗል፡፡

ለመጪው የኢሬቻ በዓል ትብብራችንና አንድነታችንን ጠብቀን ሳንዘናጋ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከተማችንን ዳግም የሰላም አምባ ለማድረግ እንድንነሳ ሲል ከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተለይም የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ ተቀብለን በማስተናገድ፣ ፍቅራችንን በማጋራት በአብሮነታችን የኢትዮጵያን ከፍታ ዳግም ልናረጋግጥና የጠላትን ሴራ በዐደባባይ ዳግም ልናከሽፍ ይገባል ብሏል መግለጫው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.