ኢመደአ እና ኢንቴል ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ኢንቴል ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በመግባቢያ ሰነዱ ኢመደአ ከኢንቴል ኮርፖሬሽን ጋር በሰው ሃይል ልማትና አቅም ግንባታ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በጥናትና ምርምር ብሎም በሳይበር ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ÷ በሳይበር ጥናትና ምርምር እንዲሁም ልማት ላይ ከኢንቴል ኮርፖሬሽን ጋር ለመስራት አስተዳደሩ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢንቴል የአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የቢዝነስ ኮንሰምሽን ዳይሬክተር ኖርቤርቶ አንቶኒዮ በበኩላቸው÷ በሳይበር ደህንነት እንዲሁም ጥናትና ምርምር ዘርፍ በኢትዮጵያ የተሻለ ተሞክሮ እና አበረታች ተግባራት እንዳዩ አንስተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአስተዳደሩ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮችን ከመደገፍ እንዲሁም የሰው ኃይል ከመገንባት አንፃር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ዳይሬክተሩ የአስተዳደሩን የዲጂታል ኤግዚቪሽን እና የታለንት ልማት ማዕከላትን መጎብኘታቸውንም ከኢመደአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡