የሀረሪ ክልል ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልላዊ መንግስት የሰላም፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነት እና የአንድነት ማሳያ ለሆነው የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላለፈ።
በመልዕክቱ ኢሬቻ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሀብት ከመሆኑም ባሻገር አንድነትን ፣ አብሮነትን እና መተባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው ብሏል።
የክልሉ መንግስትም ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ የኦሮሞን ባህል፣ እሴትና ታሪክ ለማስተዋወቅና ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፥ በተለይም ስለኢሬቻ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብሏል።
የክልሉ መንግስት የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ባሳተፈ መልኩ በሰላም እና ባማረ ሁኔታ እንደሚከበር ሙሉ እምነት እንዳለውም ገልጿል።
የኢሬቻ በዓልን ስናከብር ባህልና ወጉን በጠበቀና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ሊሆን ይገባል ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል ።
የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎችም አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጎልበት ሰላም በሚያረጋገጥ መልኩ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ ማቅረቡን ከሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡