Fana: At a Speed of Life!

በፈረንጆቹ 2030 ከፍተኛ ሙቀት ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ ያስከትላል – ተመድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለማችን በፈረንጆቹ 2030 ከከፍተኛ ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር በላይ የኢኮኖሚያ ኪሳራ እንደሚያጋጥማት ተገለጸ።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽኅፈት ቤት (ኦቻ) ሰኞ ዕለት በጋራ ያጠኑትን ሰነድ ይፋ አድርገዋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ለሙቀት መጨመር የሚኖራቸው ተጋላጭነት ይበልጥ እንደሚጨምር ነው ሠነዱ በትንበያው ያመላከተው፡፡

እንደ ሠነዱ ትንበያ ከሆነ እስከ 2050ዎቹ ድረስ የእነዚሁ ከተሞች ነዋሪዎች ቁጥር በሰባት እጥፍ ይጨምራል፡፡

በሙቀት መጨመር እንዲሁም ከዓየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ የካንሰር እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሚከሰት ሞት በአሃዝ እንደሚጨምርና በተለይም ታዳጊ ሀገራት ይበልጥ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑም ነው የተመላከተው።

በግብርናው ዘርፍ ላይም የሰብል ምርት እንዲሁም የእንስሳት እርባታ እና ተዋፅዖ ውጤቶች ውጤታማነት እንደሚቀንስ ተመላክቷል፡፡

በዓየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ የተፈጥሮ ሐብቶች መራቆት ፣ ሥደት እና የመሠረተ-ልማት ውድመቶችም ዓለማችን የምትጋፈጣቸው ችግሮች ናቸው ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2003 በአውሮፓ ሙቀት በመጨመሩ ምክንያት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ተመድ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ አስታውሷል፡፡

በፈረንጆቹ 2010 በሩሲያ በተከሰተ ሙቀት ደግሞ ተጨማሪ 55 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውም ነው የተመለከተው፡፡

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የዓየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚፈጠር የዓለም ሙቀት መጨመር ሰዎች አካባቢዎቻቸውን ለቀው እንዲሄዱ ሊያስገድድ እንደሚችልም ተመድ በትንበያው ማመላከቱን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ደግሞ ዓለማችን በፈረንጆቹ 2030 በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ የ2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራ ያጋጥማታል ብሏል።

እንደ ድርጅቱ ዘገባ ከሆነ እየጨመረ ያለው የሙቀት መጠን በየዓመቱ ዓለም ላይ በትሪሊየን ዶላር የሚቆጠር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያደርሳል።

በቀጣይ በዓለማችን ላይ ጠንከር ያለ የዓየር ንብረት ለውጥ እንደሚጠበቅ እና በኢኮኖሚ ድሃ የሆኑ ሀገራትን ይበልጥ ወደ አደጋ አፋፍ ሊገፋ እንደሚችል ከወዲሁ አስጠንቅቋል።

ተመድ የሳኅል ፣ የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ እስያ ቀጠናዎች በቀጣዮቹ አሥርት ዓመታት ለሰው ልጆች መኖሪያነት የማይመቹ አካባቢዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.