Fana: At a Speed of Life!

የወልዲያ – አላማጣ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ጥገና ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት የደረሰበት የወልዲያ – አላማጣ የባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ጥገና መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የመስመሩ መጠገን ከዓመት በላይ ኃይል ተቋርጦባቸው የቆዩ የላሊበላና ሰቆጣ ከተሞች እንዲሁም ሌሎች የዋግኸምራ ዞን አካባቢዎች የመብራት ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡

ከወልዲያ ዶሮ ግብር ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ በተደረገ ፍተሻ 50 ቦታዎች ላይ የኮንዳክተር ጉዳትና መበጣጠስ መድረሱ ተገልጿል፡፡

አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ቀደም ሲል ከባህርዳር፣ አሸጎዳ እና ኮምቦልቻ ከተዘረጉ መስመሮች ኃይል ያገኝ የነበረ ሲሆን ከባህርዳር – አላማጣ የተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር እስከሚጠገን ከኮምቦልቻ – አላማጣ ያለውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት መሥመር የመጠገን ሥራ ተጀምሯል።

ጥገናው ሲጠናቀቅ ከአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ በ66 ኪሎ ቮልት ኃይል ሲያገኙ የነበሩት የላሊበላ፣ ሰቆጣና ማይጨው መስመሮች ዳግም ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀደም ብሎ መግለጹ ይታወሳል።

አሸባሪው ህወሓት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀመው ጥቃት የትግራይና የአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አልቻሉም።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.