ኢትዮጵያ እያካሄደችው ላለው የመልሶ ማቋቋም ስራ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ኢትዮጵያ እያካሄደችው ላለው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራ ቻይና የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከቻይና ህዝብ ለውጭ ሀገራት ወዳጅነት ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር ጂያንግ ጂያንግ ጋር ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም አምባሳደር ተሾመ ÷ የኢትዮጵያ መንግስት በግጭቱ የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ተግባራዊነት የቻይና የተለመደ ትብብር እንደማይለይ ያላቸውን እምነት ገልፀው÷መንግስት ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በትብብር በመስራት በግጭቱ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን በራሷ እንድትፈታ ቻይና ለምታሳየው በመርሕ ላይ የተመሰረተ አቋምና ጠንካራ ድጋፍም የኢትዮጵያ መንግስት አድናቆት ያለው መሆኑን መግለጻቸውን በቻይና ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ጂያንግ ጂያንግ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የቻይና ስትራቴጂክ አጋር እንደመሆኗ ለጋራ ብልጽግና በትብብር ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡