Fana: At a Speed of Life!

ዲጅታል ሉዓላዊነትን በማስከበር ጥረት ውስጥ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር ወሳኝ ነው – አቶ ሰለሞን ሶካ

 

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዲጅታል ሉዓላዊነትን በማስከበር ጥረት ውስጥ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር ወሳኝ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ተናገሩ።

ዓለም አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀግ ኮንፈረንስ በባህርዳር እየተካሄደ ነው።

ለ10ኛ ጊዜ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እየተካሄደ ያለው ኮንፈረንስ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዙሪያ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት የምርምር ሀሳቦች የሚቀርቡበት ነው።

በአጠቃላይ ከቀረቡት 200 የምርምር ውጤቶች መካከል በተቋሙ የተመረጡ 60 የምርምር ስራዎች በኮንፈረንሱ ላይ እየቀረቡ መሆኑን ኢቢሲ ዘግቧል።

የኮንፈረንሱ ዓላማ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢንጂነሪንግ ዙሪያ የተሰሩ የምርምር ስራዎች ለማህበረሰቡ በሚቀርቡበት አግባብ ላይ ለመምከር ነው።

በመድረኩ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕረዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘን ጨምሮ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

ዲጅታል ሉዓላዊነትን በማስከበር ጥረት ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ እውቀትን የማሸጋገር ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ኢመደአ ከ10 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በአጋርነት እየሰራ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችሉ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማውጣት በኩልም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍላጎቷ እያደገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ በሳይበር ሴክዩሪቲ ዘርፍ ሀገሪቱ የለማ የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጂ ያስፈልጋታል ሲሉ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.