Fana: At a Speed of Life!

ከስምምነቱ ማግስት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦንድ ሽያጭ በዓለም ደረጃ በፍጥነት ጨምሯል – አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ከተደረገው የሰላም ስምምነት ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የኢትዮጵያ ‘ዩሮ ቦንድ’ ገዢ ባለሃብቶች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ መጨመሩን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አመለከቱ።

በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን ለመገንባት የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ በተገቢው ከተተገበረ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አክለው ገልጸዋል።

አቶ ዘመዴነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ የባለሃብቶችን ፍሰት ለመጨመር ከዓለም ባለሃብቶች የተበደረችው የአንድ ቢሊየን ዶላር ‘ዩሮ ቦንድ’ በጦርነቱ ምክንያት ባለሃብቶቹ ወደ ሀገሪቱ የመሄድ ፍላጎት በማጣታቸው የቦንዱ ዋጋ በዓለም ገበያ በጣም ወርዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊየን ሕዝብ ያውም አብዛኞቹ በአምራች እድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የሚገኙባት ሀገር በመሆኗ እና በአየር ንብረቷ ለባለሃብቶች ተመራጭ ሀገር ናት ያሉት አቶ ዘመዴነህ፥ የሰላም እጦቱ በባለሃብቶች ፍሰት ላይ ያስከተለው ጥቁር ጠባሳ እንዳለ ሆኖ በባለሃብቶች ፍሰት ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ መሰለፍ መቻሏን አስታውቀዋል።

ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀውና መተኪያ የሌለውን የሰው ሕይወት ያጠፋ እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ የጎዳውን ጦርነት በሰላም ከመቋጨት በላይ የሚያስደስት ነገር እንደሌለም ነው የተናገሩት።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት በሀገሪቱ ሰላም ከሰፈነ ለጦርነት የሚውል ሀብት ወደ ልማት በማዞር የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ከመቅረፍ ጎን ለጎን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳ እጅግ የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ምናልባት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ በቢሊየን ብር የሚቆጠሩ መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን ያወሱት አቶ ዘመዴነህ፥ በአንጻሩ ደግሞ በስምምነቱ ምክንያት በብድርና በእርዳታ መልክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ታስቦ የተያዙ በቢሊየን የሚቆጠሩ ገንዘቦች ሊለቀቁ ስለሚችሉ አካባቢዎቹን መልሶ ከመገንባት በዘለለ ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

ሰሞኑን ከአሜሪካ ባለሀብቶች ጋር በተደረገው ውይይትም የሀገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት ከተመለሰ የአጎዋን ችግር መፍታት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.