የፕሪቶሪያ ስምምነት ቅድመ ሁኔታ የለውም፤ ስለሆነም በስምምነቱ መሠረት ይፈፀማል – ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነት ቅድመ ሁኔታ እንደሌለውና በስምምነቱ መሠረት እንደሚፈፀም የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ገለፁ።
ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በማህበራዊ ትስስር ገፅ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ፍላጎቶችን ማጣጣም የዴሞክራሲ መርህ ነው” ብለዋል።
ለህዝብና ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ሲባል በየዕለቱ መንግስት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን አንስተዋል።
“እያንዳንዱ ሰው እንደሚመኘው ሰላምንና ብልፅግናን ማስፈን የመንግስታችን ተቀዳሚ ዓላማ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ሰላምን የምናሰፍነው በመርህ እና በህግ ነው” ብለዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለሰሜኑ ሀገራችን ክፍል መሠረት መጣሉንም በመግለፅ፥ የናይሮቢው ደግሞ የማስፈጸሚያ መሠረት ማስቀመጡን አመልክተዋል።
“ያለን ብቻኛው አማራጭ ይህንን ማስፈፀም ነው” ብለዋል።
ሁሉንም አሸናፊ ለሚያደርገው መርህ ሁሉም አካል የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።