Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ለቻይና የምታቀርበውን የጋዝ ምርት መጠን ልታሳድግ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ለቻይና የምትሸጠውን የጋዝ ምርት የአቅርቦት መጠን ልታሳድግ መሆኑን የሩሲያው የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ጋዝ ፕሮም አስታወቀ፡፡

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ አሌክሴይ ሚለር እንዳስታወቁት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 ቤጂንግ ከጠየቀችው የነዳጅ ውል ስምምነት በላይ ሞስኮ ነዳጅ ስታቀርብ መቆየቷን አንስተዋል፡፡

ሩሲያ ጋዝ ለማቅረብ በገባችው ውል መሰረት ከፈረንጆቹ  ታኅሣሥ 31 ቀን ጀምሮ ወደ ቻይና መላክ መጀመሯን ያነሱት ስራ አሰፈፃሚው፥ ከጥር 1 ጀምሮ ጋዝፕሮም ተጨማሪ ጋዝ ለቻይና ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሩሲያ በሳይቤሪያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በኩል ለእስያ ሀገራት ጋዝ የምታቀርብ ሲሆን ጋዝፕሮም ተጨማሪ የጋዝ ማጓጓዣ መንገዶችን በመጠቀም  ወደ ቻይና የሚያደርሰውን አቅርቦት የበለጠ ለማሳደግ አቅዷል ተብሏል፡፡

ጋዝፕሮም ከቤጂንግ ጋር ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን ከፍ ቢልም አጠቃላይ የወጪ ንግድ መጠኑ ከ2021 ጋር ሲነፃፀር በ 45 በመቶ ሲቀንስ የምርት መጠኑ ደግሞ በ20 በመቶ ዝቅ ማለቱን አር ቲ አስነብቧል።

ኩባንያው ሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ ለአውሮፓ ሀገራት የሚያቀርበውን ምርት ማቋረጡ እና በኖርድ ስትሪም ጋዝ የማስተላለፊያ መስመር ላይ የደረሰው ጉዳት ለወጪ ንግዱ መቀነስ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.