Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያው ኩባንያ የኔቶን ታንኮች ለሚያወድም 70 ሺህ ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ አለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ኬሚካል አምራች ኩባንያ ፎረስ የኔቶን ታንኮች ለሚያወድም 70 ሺህ ዶላር ሽልማት ማቅረቡን ገለጸ፡፡

ኩባንያው በዩክሬን ኤም 1 አብራምስ እና ሊዮፓርድ- 2 ታንኮችን ለሚያወደሙ ወታደሮች ጉርሻ እንደሚሰጥ ነው ያስታወቀው።

ኩባንያው ይህን ያለው ባለፈው ሳምንት ዋሺንግተን እና በርሊን ታንኮቹን ለኪየቭ ለመስጠት ከወሰኑ በኋላ ነው።

የጀርመን ሊዮፓርድ- 2 ወይም የአሜሪካው ኤም 1 አብራምስ የጦር ታንክን የሚያወድም ወይም የሚማርክ ወታደር የገንዘብ ሽልማት ያገኛል ሲል ኩባንያው በድረ-ገጹ ባሰፈረው መልዕክት አስታውቋል።

ኩባንያው የመጀመሪያውን አንድ ታንክ ለሚያወድም የ 5 ሚሊየን ሩብል ወይም 70 ሺህ 700 ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ ነው የገለጸው።

ለእያንዳንዱ ቀጣይ ድሎችም 500 ሺህ ሩብል ወይም 7 ሺህ 70 ዶላር እንደሚሰጥ ጠቁሟል።

ዩክሬን ኤፍ-15 እና ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን የምታገኝ ከሆነ የመጀመሪያውን አውሮፕን ለጣለ የ15 ሚሊየን ሩብል ወይም 212 ሺህ 100 ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ማለቱን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

በሩሲያ ትላላቅ የንግድ ማህበረሰቦች የአሜሪካ እና የጀርመን የጦር ታንኮችን ለሚያወድም 10 ሚሊየን ሩብል ወይም 143 ሺህ 900 ዶላር ሽልማት ማዘጋጀታቸውን በሀገሪቱ አንጋፋ ተዋናይ ኢቫን ኦክሎቢስቲን በኩል በትናንትናው ዕለት ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.