Fana: At a Speed of Life!

በቱርክ እና ሶሪያ ድንበር አዲስ ርዕደ መሬት ተከሰተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ እና ሶሪያ ድንበር በአዲስ ከባድ ርዕደ መሬት ተመታ፡፡

በቱርክ ሃታይ ግዛት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 4 እና 5 ነጥብ 8 የተለካ አዲስ ርዕደ መሬት መከሰቱ ተሰምቷል።

እስካሁን በርዕደ መሬቱ ሳቢያ እስከ 5 ሰዎች ለህልፈት ሳይዳረጉ አልቀረም ነው የተባለው።

የአሁኑ አደጋ ከ45 ሺህ በላይ የቱርክ እና ሶሪያ ዜጎችን ለህልፈት የዳረገው ከባድ ርዕደ መሬት ከተከሰተ ሁለት ሳምንታት በኋላ በድጋሚ የተከሰተ ነው።

የሀገሪቱ የዜና አገልግሎት (አናዶሉ) እንደዘገበው በአዲሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በርካታ ሕንፃዎች ወድመዋል።

የቱርክ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ዜጎች ከሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ እንዲርቁ አሳስበዋል።

እስካሁን ለህልፈት ከተዳረጉት በተጨማሪ 213 የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውን ነው የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሉ የተናሩት።

በርዕደ መሬቱ ሳቢያ ከቱርክ ባለፈ በሶሪያ በርካታ ህንጻዎች መውደማቸውን አልጀዚራ እማኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የትናንቱ ርዕደ መሬት ሶሪያን ጨምሮ ዮርዳኖስ፣ ኢራቅ፣ ፍልስጤም እና እስራኤል ድረስ መሰማቱን የአር ቲ ዘገባ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.