Fana: At a Speed of Life!

ግብጽ ሰሞኑን እየተከተለችው ያለው ተንኳሽ አካሄድ መሬት ላይ ያለውን እውነት አይቀይረውም – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብጽ ሰሞኑን እየተከተለችው ያለው ተንኳሽ አካሄድ መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይቀይረውም ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡

በኢትዮ-ዓረብ ግንኙነቶች ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል÷ኢትዮጵያ ካሁን ቀደም እንዳደረገችው ሁሉ በ4ኛው ሙሌት መሬት ላይ ያለውን ስራ ገቢራዊ እያደረጉ መቀጠል የሁሉም ጫናዎች መመከቻ አቅሟ ነው ብለዋል፡፡

የግብጽ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ከተለመደው የአዞ እንባ አፍሳሽነት ባህሪዋ የሚመነጭ ነው ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የባህረ ሰላጤው ሀገራት ባለሃብቶች እንደ ሳዑዲ፣ ኩዌት፣ ኦማን እና ኳታር፣ በግብጽ የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፋቸውን አብራርተዋል።

ግብጽ ÷ ኢትዮጵያ በኅዳሴው ግድብ ስኬታማ ከሆነች እና የመስኖ ምርቶችን ካለማች ሀገራቱን ትወሰድብኛለች የሚል ስጋት እንዳላትም አንስተዋል፡፡

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው አህመድ አሊ በበኩላቸው÷ግብጻውያኑ አጀንዳውን የመዘዙት ለቀጣይ የውስጥ ፖለቲካቸው መደላድል ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን አብራርተዋል።

የግብጽ የሰሞኑ ቃላት ውርወራ ብዙ ለውጥ እንደማያመጣ የገለጹት ደግሞ በዋቻሞ የኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ዲሞክራሲ ጴጥሮስ ናቸው፡፡

ሰርጎ የመግባትና የውስጥ ፖለቲካን ለዕኩይ አላማ የመጠቀም ተለምዶ ስላለ፣ ሐገራዊ ሰላም እና አንድነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በታደሰ ሽፈራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.