Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ተሸካሚ የውሃ ውስጥ ድሮን ሙከራ አደረገች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ኒውክሌር የመሸከም አቅም ያለው የውሃ ውስጥ ሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላን (ድሮን) ሙከራ ማካሄዳቸውን የሀገሪቱ የዜና ጣቢያ ገለጸ፡፡

የውሃ ውስጥ ድሮኑ ከ80 እስከ 150 ሜትር ባለ ጥልቀት ውስጥ በውሃ ውስጥ ከ59 ሰአታት በላይ ከተጓዘ በኋላ በምስራቃዊ የባህር ዳርቻ መፈንዳቱን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

ድሮኑ በውሃ ውስጥ ከተተኮሰ በኋላ “የራዲዮአክቲቭ ማዕበል” ሊያስነሳ የሚችል መሆኑንም ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ይህንን ሙከራ በበላይነት የመሩ ሲሆን አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ “የሰሜን ኮሪያ ያልተገደበ የኒውክሌር ጦርነትን የመከላከል አቅም በከፍተኛ ፍጥነት እየተጠናከረ መሆኑን እንዲገነዘቡ” ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ፖሲዶን ከተሰኙት የሩሲያ የውሃ ውስጥ ተተኳሾች ጋር እንደሚመሳሰሉ የተነገረላቸው የሰሜን ኮሪያ የቅርብ ጊዜ መሳሪያዎች የባሕር ላይ ማዕበል በማስነሳት በአሜሪካ የባህር ዳርቻ ከተሞችን ሊያወድሙ ይችላሉም ነው የተባለው።

“ሚስጥራዊው መሳሪያ” ማክሰኞ ከደቡብ ሃምጊዮንግ ግዛት ወጣ ብሎ በሚገኘው ውሃ ውስጥ መቀመጡም ነው የተነገረው።

“ሃኤይል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የጦር መሳሪያ የጠላት መርከቦችን እና ወደቦችን በከፍተኛ የራዲዮአክቲቭ ሞገድ ለማጥቃት ታስቦ የተነደፈ መሆኑንም የሀገሪቱ የዜና ምንጭ አስነብቧል፡፡

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ትልቅ የተባለ የጋራ ልምምዳቸውን ባለፈው ረቡዕ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ በኮሪያ ልሳነ ምድር ዳግም ውጥረት መንገሱ ይነገራል።

ይሁንና የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ-ዮል÷ ሰሜን ኮሪያ በግዴለሽነት ለምታደርገው ትንኮሳ ዋጋ ትከፍላለች ሲሉ ተደምጠዋል።

ፒዮንግያንግ ይህን የውሃ ውስጥ ኒውክሌር ተሸካሚ መሳሪያ በማንኛውም የባህር ዳርቻ እና ወደብ ላይ ልትጠቀመው እንደምትችል ገልጻለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.