Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል ለምታከናውናቸው ተግባራት የቴክኒክ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ተመድ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል የምታከናውናቸውን ተግባራት ለማጠናከር የሚደረገው የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደገኛ እጽና ወንጀል መከላከል ቢሮ ገለጸ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደገኛ እጽና ወንጀል መከላከል ቢሮ ከፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሙስናን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ እንደገለጹት ፥ መንግሥት ሙስናን በመዋጋት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተለያዩ ተግባራትን እያከነወነ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታትም መንግሥት የሙስናን አስከፊነት በመገንዘብ በሙስና ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች በሕግ ተጠያቂ እያደረገ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅትም ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ ተጠያቂነትን ለማስፈን በተጠናከረ ሁኔታ በአዲስ ስልትና ቁርጠኝነት መቀጠሉን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በሙስና ወንጀል ተግባር የሚሳተፉ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ለፍትህ በማቅረብ ወንጀሉን የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትም የመንግሥት ተቋማት ውስጣዊ አሰራሮችን በመፈተሽ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሰሩ ሥራዎችን በማውገዝ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የተመድ አደገኛ እጽና ወንጀል መከላከል ቢሮ ኃላፊ ሃና ኤልሳቤት በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ ሙስናን በመከላከል የምጣኔ ሃብት እድገት ለማምጣት በምታከናውናቸው ተግባራት ድርጅቱ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በግሉ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እየተካሄደ ባለው ውይይት ምሁራን፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችና የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.