Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕ የወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የመጀመሪያው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞዋን የወሲብ ፊልም ተዋናይ ስቶርሚ ዳንኤልስን ዝም ለማሰኘት 130 ሺህ ዶላር ከፍለዋል በሚል ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑ ተሰማ።

ትራምፕ በፈረንጆቹ 2016 በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ከመሆናቸው ቀደም ብሎ ለግለሰቧ የከፈሉት ገንዘብ አለ በሚል በኒውዮርክ ጠበቆች ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል።

ምርመራው ትራምፕ ከቀድሞዋ የወሲብ ፊልም ተዋናይ ጋር የፈጸሙት ጾታዊ ግንኙነት ይፋ እንዳይሆን ገንዘብ ከፍለዋል በሚል ነው ሲካሄድ የቆየው።

በመዝገብ ስሟ ስቴፈኒ ክሊፎርድ በመባል የምትታወቀው አሜሪካዊት የቀድሞ የወሲብ ፊልም ተዋናይ ከትራምፕ ጋር በፈረንጆቹ 2006 በገቢ ማሰባሰቢያ የጎልፍ ጨዋታ ላይ መገናኘታቸውን ተናግራለች።

አያይዛም ከትራምፕ ጋር በካሊፎርኒያ እና ኔቫዳ መካከል በሚገኘው የላሆይ ሐይቅ ቅንጡ ሪዞርት ውስጥ ጾታዊ ግንኙነት እንደነበራቸው አስረድታለች።

በፈረንጆቹ 2016 ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀናት ቀደም ብሎ የትራምፕ ጠበቃ ማይክል ኮኸን ጉዳዩን ለማንም እንዳትናገር 130 ሺህ ዶላር እንደከፈላትም ነው የተናገረችው።

ከዚያን ጊዜ በኋላም “የትራምፕን ጉዳይ” እንድትተወውና ጉዳዩን ከመናገር እንድትቆጠብ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደደረሳት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሚደረገው ማጣራት በሰጠችው ቃለ ምልልስ ላይ ገልጻለች።

ትራምፕ ግለሰቧን ዝም ለማስባል የከፈሉት ገንዘብ ህገ ወጥ ባይሆንም የምርጫ ቀናት በተቃረበበት ወቅት የተከፈለ በመሆኑ “በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል” በሚል እንደዘመቻ ማጭበርበር እንደሚታይም ነው የተገለጸው።

ከዚህ ባለፈም ትራምፕ ክፍያው በህጋዊ መንገድ ቢፈጽሙም የተፈጸመው ክፍያ ግን ግለሰቧ ዝም እንድትል ሳይሆን ለንግድ ስራ ወጪ በሚል የተፈጸመ በመሆኑ፥ በኒውዮርክ የንግድ መዝገቦችን ማጭበርበር ህገወጥ በመሆኑ ጉዳዩ በህግ እንዲታይ አድርጎታል።

ትራምፕ በመጪው ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸውን እንደሚከታተሉ እና በኒውዮርክ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል፡፡

የ76 ዓመቱ ትራምፕ ጥፋታቸውን የካዱ ሲሆን÷ ክሱን “ፖለቲካዊ ጭቆና” ነው ሲሉም ተቃውመዋል።

የሚቀርብባቸው የክስ ዝርዝር እስካሁን ይፋ ባይደረግም÷ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ትራምፕ ከንግድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ከሃያ በላይ ክሶች ሊቀርብባቸው እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ሪፐብሊካኖች ክሱን “ከባድ ቁጣ” ያሉት ሲሆን÷ ዴሞክራቶች ደግሞ ማንም ከህግ በላይ አይደለም በሚል የህግ አካሄዱን ደግፈው መታየታቸውን ነው ዘገባዎች የሚያመላክቱት።

በትራምፕ ላይ የቀረበውን ክስ ሲመሩ የቆዩት የማንሃተን ዐቃቤ ሕግ አልቪን ብራግ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ስር ስለሚውሉበት ሁኔታ ከትራምፕ ጠበቆች ጋር ንግግር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በአሜሪካ ታሪክ በሥልጣን ላይ ባለም ይሁን በቀድሞ ፕሬዚዳንት ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቶ የማያውቅ ሲሆን፥ ትራምፕ የወንጀል ክስ የሚቀርብባቸው የመጀመሪያው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.