Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን ማሳያ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተከታታይ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከቀውስ ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነቶችን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ ከሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ ጋር ስኬታማ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በ1956 ዓ.ም የተጀመረውን የሀገራቱን ግንኙነት ለማዳበር በሚያስችሉ ጉዳዮች እንዲሁም በአካባቢያዊ እና በባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ነው የገለጹት፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን÷ ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ መግለጻቸውን ነው አንስተዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ችግር ለመፍታት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ትግበራ በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጨባጭ እና ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ በበኩላቸው÷በኢኮኖሚ እና በሲቪል አቪየሽን መስክ በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት እንዲደረግ ላቀረቡት ጥያቄ ኢትዮጵያ ይሁንታ ማሳየቷንም አምባሳደር መለስ  አብራርተዋል፡፡

ሀንጋሪ በምትታወቅበት በውኃ ልማት፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በሌሎች ዘርፎችም ትብብራቸውን ለማጠናከር መነጋገራቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ የማስረዳት፣ የማለዘብ እና ወዳጅ የማብዛት ስትራቴጂን በተቀናጀ ሁኔታ እየተገበረች መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በጎረቤት ሀገራት እና በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት መስፈን የበኩሏን ሚና ለመወጣት ያላትን ሚና በተመለከተም ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.