Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የንግድ ሕጓን በመከለስ አዲስ የኢንቨስትመንት አዋጅ ደንግጋለች- አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መከለሱንና አዲስ የኢንቨስትመንት አዋጅ መደንገጉን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስታወቁ፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትና ባለሐብቶች የሚሳተፉበት “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023” ፎረም ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

አቶ አሕመድ ሽዴ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ውስጥ የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሐብቶችም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የመንግስትን የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል የማዞር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በኩል የንግዱን ዘርፍ ለማሳለጥ ማዕከላዊ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

በበርካታ የዓለም ክፍል መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ ዓየር መንገድም ባለሐብቶች ወደ ተለያዩ ሀገራት ምርታቸውን በማድረስ ረገድ ሌላኛው ምቹ አጋጣሚ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

አቶ አሕመድ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ፣ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እና በኢትዮጵያ እንዲቆዩ ለማድረግ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ አምራች የሰው ኃይል ያላት እና የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ አምሥት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኢንቨስት መንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ÷የውጭ ባለሐብቶች መዋዕለ-ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ እንዲወስኑ ይረዳቸው ዘንድ ሀገሪቷ ያላትን ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እና መዳረሻዎች እንዲመለከቱ ጋብዘዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ላይ አጭር ገለጻ አቅርበው ሀገሪቷ ሁለተኛውን የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመተግበር ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

በፎረሙ የተለያዩ የመንግስት ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን እና አመራሮች ያሳተፈ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.