Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል ካቢኔና ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል መንግስት ካቢኔና ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተዘጋጀ ፅሁፍ ላይ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ውይይቱን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር  ሙስጠፌ መሀመድ የመሩ ሲሆን÷ ከተዳሰሱ ወቅታዊ ጉዳዮች መካከል በክልሉ የልማት ሥራዎች በሚጠናከርበት ሁኔታ ፣ በከተማ ግብርናን ማስፋፋት፣ በምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ አረንጓዴ አሻራን ማስቀጠል እንዲሁም የክልሉን ገቢ ማሳደግ የሚሉት ጉዳዮች ይገኙበታል።

በውይይቱ  የሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ለማሳካት ዜጎች ፅንፈኝነትን በጋራ በመዋጋት ለልማት በተለይ የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና እየጣለ ያለውን ዝናብ  በመጠቀም የአረንጓዴ አሻራን ለማሳካት ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል ተብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የልማት ፕሮግራሞችን ወደ ተጨባጭ ተግባር በመለወጥ የክልሉን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነና ለታቀዱ ትላልቅ ሀገራዊ ስኬቶች ክልሉ አመርቂ ሥራዎችን በመስራት ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል በውይይት መድረኩ ላይ ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በሰጡት የስራ መመሪያና አቅጣጫ አማካኝነት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሁሉም የካቢኔና ከፍተኛ አመራሮች እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው የመዋቅር እርከን በመውረድ ህዝቡን በማወያየት እና የህዝቡን የኑሮና የልማት ጥያቄዎችን አዳምጠው ለቀጣይ መልስ የሚሹ ነጥቦችን ይዘው እንዲመጡ ተወስኗል።

ለውይይት ከቀረቡት ጉዳዮች መካከልም የክልሉ ልዩ ሀይል እንደገና መልሶ የማደራጀት አስፈላጊነት ይገኝበታል።

በዚህም  ካቢኔውና ሌላው አመራር የክልሉ ልዩ ሀይል ከተቋቋመለት አላማ አንፃር እጅጉን አኩሪ ስራዎችን መስራቱ ተገልፆ  ላቅ ያለ ክብርና ምስጋና ቀርቦለታል።

በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ባለው የፀጥታ መዋቅር ሪፎርም አማካኝነት ልዩ ሀይሉ እንደገና ወደ ሀገሪቱ የፀጥታ መዋቅሮች እና ወደ ክልሉ መደበኛ ፖሊስ በሚደራጅበት በአሁኑ ወቅትም ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ በሚሰማራበት ተልዕኮ ሁሉ ድልን በማስመዝገብ የህዝብና የሀገር አለኝታነቱን እንደ ሚያስቀጥል አመራሩ በጋራ አስምሮበታል።

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት የመደበኛ ፖሊስ ኃይልን በማጠናከር በልዩ ሀይሉ አማካኝነት ይሰሩ የነበሩ የፀጥታ ስራዎች በመደበኛ ፖሊስም ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

ይህ ውይይት ወደ ታችኛው የመዋቅር እርከን በማውረድ ሰፊ  የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚዘጁ የብልፅግና ፓርቲ ሶማሌ ክልል ቅ/ፅ/ቤት ሀላፊ  መሀመድ ሻሌ (ኢ/ር) መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.