Fana: At a Speed of Life!

በቱርክ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ድምፅ መስጠት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ ድምፅ መስጠት ተጀምሯል፡፡

ለሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ሕዝብ ያገለግሉኛል ያላቸውን ፕሬዚዳንት እና የፓርላማ አባላት ለመምረጥ ከ64 ነጥብ 1ሚሊየን በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል።

በዚህም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ በማምራት መምረጥ መጀመራቸውን የዘገበው አናዶሉ ነው።

ከ64ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የተመዘገቡ መራጮች ውስጥም ከ1ነጥብ 76 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ከሀገሪቱ ውጭ ያሉ ሲሆኑ ፥ 4ነጥብ 9 ሚሊየኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መራጮች እንደሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

191 ሺህ 885 ድምጽ መስጫ ሳጥኖችም ለዚሁ ምርጫ ተዘጋጅተዋል ተብሏል።

እያንዳንዱ መራጭ ሁለት ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን ፥ አንደኛው ለፕሬዚዳንቱ ፤ ሁለተኛው ደግሞ ለፓርላማ አባላት ነው ፡፡

መራጮች ድጋሚ ለመመረጥ ከሚወዳደሩት ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን፣ ዋና ተቃዋሚያቸው ከማል ኪሊዳሮግሉ እና ሲናን ኦጋን መካከል ይሆነኛል ያሉትን ይመርጣሉ።

ሌላው ለፕሬዚዳንትነት ሲፎካከር ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት ሙሃረም ኢንስ ባሳለፍነው ሐሙስ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸው ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም በምርጫው ከ30 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ150 በላይ የፓርላማ እጩዎች ይወዳደራሉም ተብሏል።

በምርጫው ውስጥ አምሥት የመድበለ ፓርቲ ቡድኖች ያሉ ሲሆን ፥ እነሱም ፡- የሕዝብ ጥምረት፣ የብሔር ጥምረት፣ የቀድሞ አባቶች ጥምረት፣ የሠራተኛና የነፃነት ጥምረት እንዲሁም የሶሻሊስት ኃይሎች ኅብረት በመባል ይታወቃሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.