Fana: At a Speed of Life!

በጋራ ፍትኃዊና አካታች ዓለም እንገነባለን – ቭላድሜር ፑቲን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በመተባበር ፍትኃዊና አካታች ዓለም እንደምትገነባ ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ገለጹ፡፡

ፑቲን አያይዘውም ከሩሲያ ጋር ለመተባበር ዝግጁ የሆኑ ሀገራት ጠላቶች እና ፈተናዎች የጋራ በመሆናቸው በጥምረት ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ከሀገራት ለተውጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህን ያሉት በዛሬው 11ኛ ዓለም አቀፍ የደኅንነት ጉዳዮች ስብሰባ ላይ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡

“አንድ ከሆንን በእርግጠኝነት ፍትኃዊ እና አካታች ዓለም እንመሰርታለን፤ አግላይ አስተሳሰብ፣ ኢ-ፍትኃዊ የሐብት ክፍፍል እና የእጅ አዙር የአገዛዝ ሥርዓት ታሪክ ይሆናልም” ነው ያሉት፡፡

ሩሲያ በተለያዩ ቀጣናዎች እና አኅጉራት ወዳጆች እንዳሏትና ሐሳቡንም እንደሚጋሩት አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም እስያ ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ የሩሲያ ታሪካዊ፣ ጠንካራ እና ታማኝ ወዳጆች ናቸው ሲሉም ነው የጠቀሷቸው፡፡

ፑቲን ሀገራቸው ወዳጆቿን በምትችለው ሁሉ ለማጠናከር እና ከጎናቸው ለመቆም ዝግጁ መሆኗንም ነው የተናገሩት፡፡

አሜሪካ እና አጋሮቿ ዓለምን ለመቆጣጠር የጦር ኃይል እንደሚያደራጁ ፣ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገቡ እንዲሁም የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ዓለምአቀፉን የኃይልና የምግብ ቀውስ እንደሚጠቀሙበትም አውስተዋል፡፡

በእነሱ ምክንያት በዓለማችን የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶች እና ቀውሶች እየጨመሩ መምጣታቸውንም ነው ፑቲን የገለጹት።

“ዓለም ላይ ለሚታየው ዘርፈ ብዙ ችግርና የተረጋጋ አካባቢን ለመፍጠር ብሎም ሴራቸውን በጥምረት ለመታገል እንተባበር” ሲሉም ለሀገራት ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.