Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን በጋራ ለመከላከል መከሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል በአዲስ አበባ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም ÷ በውይይቱ ቀጠናው ለሽብር ወንጀል ተጋላጭ በመሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ ህገ-ወጥ ገንዘብ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሌሎች የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል።

የድርጅቱን የመሪነት ሚና ኢትዮጵያ ከተረከበችበት ጀምሮ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተካሄደ ያለው የሪፎርም ስራ ሁሉም የቀጠናው አባል ሀገራት ወደ ራሳቸው ወስደው ለመተግበር በጉባዔው ላይ በአንድ ድምፅ መወሰናቸው ህብረቱን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም የመረጃ ልውውጥ ሂደቱ እና የወንጀልን መከላከል አቅም እየዳበረ እንደመጣ መገለጹን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

በአልሸባብ የሚፈፀሙ የሽብር ወንጀሎች በምስራቅ አፍሪካ እንዳይስፋፉ የቀጠናውን ሀገራት በማስተባበር ከጀግናው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጋር በመሆን ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጀነራል ደመላሽ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት ያላት በመሆኗ ከሀገር ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ለማምለጥ የሚጥሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከሌሎች ሀገራት ወንጀል ፈፅመው ወደ ሀገራችን ለመግባት የሚሞክሩ ተጠርጣሪዎችን በተጠናከረ የመረጃ ልውውጥ ወንጀለኞች ሳያመልጡ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ለህግ እንደሚቀርቡ ሠፊ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሽብርተኝነት፣ ህገ-ወጥ ጦር መሣሪያ፣ህገ-ወጥ የገንዘብ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም በሌሎች የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በተለይም በምስራቅ አፍሪካ በየትኛውም አካባቢ መደበቅ እንደማይችሉ በቅርቡ በአባል ሀገራት ቅንጅት የተካሄዱ ኦፕሬሽኖች ጉልህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.