Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የዛፓሪዢዬ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን በተመለከተ አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዛፓሪዢዬ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ቀጣይነት ያለው የውሃ አቅርቦት ማግኘት እንደሚገባው ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ አሳሰበ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ እንደገለፁት፥ የአውሮፓ ትልቁ  የአቶሚክ ሃይል ጣቢያ የሆነው ማመንጫው ስድስት ዋና ዋና መሳሪያዎቹን ለማቀዝቀዝ በካኮቭካ የውሃ ግድብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የካኮቭካ ግድብ ማክሰኞ ማለዳ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የውሃው መጠን በ2 ነጥብ 8 ሜትር ቀንሷል ነው ያሉት።

የውሃው መጠን አንዴ ከ12 ነጥብ 7 ሜትር በታች ከሆነ የሃይል ጣቢያው ከውኃ ማጠራቀሚያው ውሃ መሳብ አይችልም ሲሉም ግሮሲ አስጠንቅቀዋል።

የግድቡ አጠቃላይ የጉዳት መጠን እንደማይታወቅ  የገለፁት ዳይሬክተሩ፥  አሁን ባለው ፍጥነት በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የውሃው መጠን በሰዓት ከ5 እስከ 7 ሴንቲ ሜትር  ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ግሮሲ በቦታው ላይ የሚገኙ የኤጀንሲውን ባለሙያዎች መረጃ በመጥቀስ የዛፓሪዢዬ የኒውክሌር ጣቢያ የውሃ ማጠራቀሚያውን በመገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሚቀጥለው ሳምንትም ተጨማሪ ባለሙያዎችን ወደ ስፍራው ለመላክ እንደታሰበ መግለፃቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

በቀጠናው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በጨመረበት በዚህ ሰዓት፥ ከምንጊዜውም በላይ የኒውክሌር አደጋን እና በሰዎች እና በአካባቢ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ ለመከላከል የአቶሚክ ሃይል ጣቢያ ባለሙያዎች በዛፓሪዢዬ መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው ሲሉም ግሮሲ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.