Fana: At a Speed of Life!

የጊኒዎርም በሽታ በጋምቤላ ክልል ዳግም በወረርሽኝ መልክ ተከሰተ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 20፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የጊኒዎርም በሽታ በጋምቤላ ክልል ዳግም በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን  የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋትሉዋክ እንዳሉት ከሀገሪቱ  ብሎም ከክልሉ የጊኒዎርም በሽታን ለማጥፋት የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የጊኒዎርም በሽታ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ ጀምሮ ጨርሶ ለማጥፋት በተከናወኑ ተግባራትም አበረታች ውጤት የታየ ቢሆንም÷ ወረርሽኙ ዳግመኛ ተከስቶ በጎግ ወረዳ ጎግ ዲፓች ቀበሌ ዱሌ ንዑስ መንደር በሰባት ሰዎች ላይ ተከስቷል።

በመሆኑም ላለፉት 27 ወራት በሽታው በውሾችና በዝንጀሮ ላይ ሲከሰት እንደነበር ገልፀው በአሁኑ ሰዓት በወረርሽኝ መልክ በሰባት ሰዎች ላይ መከሰቱን አመልክተዋል።

ሀላፊው በሽታው ዳግም ሊያገረሽ የቻለው በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት በመፈጠሩም ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በሽታውን እንዲከላከል የቅኝት ስራ መሰራቱንና የንፁህ መጠጥ ውሃ ባልተዳረሰት አካባቢ ውሃን አጣርተው እንዲጠቀሙ የውሃ ማጣሪያ ቁሳቁስ እንዲሁም የግንዛቤ ማሳደግ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

በካርተር ሴንተር ጊኒዎርም ማጥፊያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ አራጋው ላመስግን በበኩላቸው÷ ካርተር ሴንተር ከጤና ጥበቃና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ጊኒዎርምን የማጥፋት ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት 27 ወራት በሽታው በሰዎች ላይ ሳይከሰት መቆየቱንና በውሾችና በዝንጀሮ ላይ ሲከሰት እንደነበር አስታውሰው ይህም በሽታውን ለመቆጣጠር ውስብስብ እንዳደረገው አመልክተዋል።

በሽታው በሀገር አቀፍ ደረጃ በጋምቤላ ክልል ብቻ እንዳልጠፋ የጠቆሙት አቶ አራጋው በቀጣይ ሀገሪቱን ከበሽታው ነፃ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የቀበሌው ነዋሪዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ስለበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው ጠቁመው÷ በሽታው ከሁለት ዓመታት በላይ በሰዎች ላይ አለመከሰቱ መዘናጋትን እንደፈጠረ ተናግረዋል።

በቀጣይም በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጣቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ወደ ተግባር በመቀየር ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከበሽታው እንደሚጠብቁ  መግለጻቸውንከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.