Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ስታዲየም በመጪው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚጀምር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ስታዲየም በመጪው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚጀምር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ቀጄላ መርዳሳ የአዲስ አበባ ስታዲየም የግንባታ ሒደትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለፁት÷በ2013 ዓ.ም የእድሳት ስራው የተጀመረው የአዲስ አብባ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡

የስታዲየሙ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ 65 በመቶ መድረሱን የገለፁት ሚኒስትሩ÷ በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

አሁን ላይም የተመልካች መቀመጫ ወንበር፣ የኤሌክትሪክና የውሃ መስመር  ስራ እንዲሁም የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ  እንደሚገኝ አንስተዋል።

የስታዲየሙን ትራክ የማንጠፍ ስራ  በቀጣይ ተጨማሪ በጀት ተይዞለት የሚከናወን መሆኑ  ያስረዱት አቶ ቀጄላ÷የውስጥ እድሳት ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ የዙሪያው ግንባታ ስራ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በወርቅነህ ጋሻሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.