Fana: At a Speed of Life!

ፋሲል ከነማ ተጫዋቾች እንዳያዘዋውር ታገደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከስምንት ቀናት በኋላ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ተጫዋች እንዳያስፈርሙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አሳልፏል።

 

ክለቡ የታገደው ከቀድሞ አሰልጣኙ ኃይሉ ነጋሽ የደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የተወሰነበትን ውሳኔ ተፈጻሚ ባለማድረጉ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል።

 

ያለፉትን ዓመታት በፋሲል ከነማ ምክትል አሠልጣኝነት ግልጋሎት ሲሰጡ የነበሩት ኃይሉ ነጋሽ ዓምና ከሁለተኛው ዙር ውድድር ጀምሮ ክለቡን በጊዜያዊ ከዛም በዋና አሠልጣኝነት ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል።

 

ዘንድሮ አሠልጣኙ 12 ሳምንታት በላይ ሳያሰለጥኑ 7 ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታቸውን ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ከማድረጋቸው ከአንድ ቀን በፊት ከክለቡ እንዲለያዩ መደረጉ አይዘነጋም።

 

አሠልጣኙ ጉዳዩን ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ወስደውት የነበረ ሲሆን ኮሚቴውም ክለቡ አሠልጣኙ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ለአሠልጣኙ ያልተከፈላቸው ደመወዝ እንዲሰጥ እና ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ አልያም እስከ ውላቸው ማብቂያ ድረስ ያላቸው ደመወዝ እንዲከፈላቸው ወስኖ ነበር።

 

ይህ ውሳኔ አግባብ አይደለም በሚል ክለቡ ይግባኝ ቢጠይቅም ይግባኙ ውድቅ ተደርጓል።

 

አሁን ደግሞ በፍትህ አካል የተወሰነውን ውሳኔ ክለቡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ተፈፃሚ ባለማድረጉ ከተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እንደታገደ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.