Fana: At a Speed of Life!

ባንኩ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር የሚረዱ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር ለማስቻል የሚረዱ ፈርጀ ብዙ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ባንክ ተገኝቶ ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም ÷ ባንኩ የዋጋ ንረት ከመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ አማራጭ ዘርፎችን ከማብዛት፣ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ከመዘርጋት፣ የፋይናንስ አካታችነት ከማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ከማጎልበት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ተብሏል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሆኑ የግልና የመንግስት ባንኮች በብዛት በባንክ ኢንዱስትሪው ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

ባንኮቹ ገበያው ላይ የሚያደረጉት የገበያ ውድድር ጤናማ፣ ሕብረተሰብን እና ሀገርን እንዲጠቅም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይገባዋልም ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው እንደገለጹት÷ ባንኩ በቅርቡ የወሰዳቸው የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች የዋጋ ንረትን ከማርገብ፣ የባንክ ብድር ዕድገትን በመግታትና የመንግሥትን የቀጥታ ብድር መጠን በመቀነስ ረገድ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡

ከፋይናንስ ጤናማነት መለኪያዎች አንጻር ሲገመገም ከቅርንጫፎች ብዛት፣ ከተቀማጭ የገንዘብ መጠን ፣ በተከፈቱ አካውንቶች ብዛትና የብድር አሰጣጥ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ፣ ትርፋማ እና የተረጋጋ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.