Fana: At a Speed of Life!

ሐሰተኛና አፀያፊ የፈጠራ ታሪክ እያሰራጩ ህዝብን የሚያደናግሩ ዩቲዩበሮችን በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከማህበረሰቡ ወግና ባህል ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ሐሰተኛ እና አፀያፊ የፈጠራ ታሪክ እያሰራጩ ህዝብን የሚያደናግሩ ዩቲዩበሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 አንድ ህንፃ ላይ ቢሮ ተከራይተው የተለያዩ የዩቲዩብ ገፆችን በመክፈት የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና የሚጎዱ የፈጠራ ታሪክ በማሰራጨት የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በህዝብ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል ተይዘው በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እየተጣራ ይገኛል ተብሏል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል መቅደስ መብራት መኮንን የተባለችው ግለሰብ ሮሄ፣ ልዩነት፣ ጣዕም፣ አዲስ አለም፣ ዘይቤ፣ ህይወት፣ እይታ እና ዩኒት ህይወት የተባሉ የዩቲዩብ ገፆችን በመክፈት በስራ አስኪያጅነት ስትመራ የነበረች ናት ተብሏል፡፡

ብሩክ ወርቅነህ ጌታሰው የተባለ ግለሰብ ደግሞ ገፆቹን በምክትል ስራ አስኪያጅነት እና በአስተባባሪነት ሲመራ የነበረ ሲሆን ናትናኤል አበራ በቀለ፣ እየሩሳሌም አስማረ ምህረት እና ምህረት ያሲን ቲጋ የተባሉት ግለሰቦች ደግሞ በፕሮግራም አቅራቢነት እንዲሁም ናትናኤል ዮሃንስ አሸነፍ በካሜራ ባለሙያነት ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ስምንት የዩቲዩብ ገፆች በተጨማሪ ክህሎት እና ሲንግል የተባሉ ሌሎች ሁለት የዩቲዩብ ገፆችም በዚያው ህንፃ ላይ የፈጠራ ወሬ ሲፈበርኩ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ተከራይተው በሚሰሩበት ቢሮ ላይ በህግ አግባብ ባደረገው ብርበራ የፈጠራ ወሬ ለመቅረፅ እና ለማሰራጨት የሚጠቀሙባቸው የኤሌክትሮኒክ እቃዎች ተይዘዋል፡፡

ግለሰቦቹ መረጃውን ለማሰራጨት የሚያስችል ከሚመለከተው አካል የተሰጠ የህጋዊነት ማረጋገጫም ሆነ ፈቃድ እንደሌላቸው በምርመራው ሂደት መረጋገጡንም ከየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሃሰተኛ እና የፈጠራ ወሬዎቹን የሚያሰራጩት ታሪኩን ለሚተውኑላቸው ግለሰቦች ገንዘብ በመክፈል ሲሆን÷ በወቅቱ ጉዳዩን በጥልቀት ሳይረዱ እና መረጃው ሳይኖራቸው የማያውቁትን የፈጠራ ታሪክ ሊሰሩ ለቀረፃ ስራ የተጠሩ ሌሎች ሶስት ሰዎችን ፖሊስ አግኝቷል፡፡

መሰል የውሽት ታሪኮችን በማሰራጨት በህብረተሰቡ ላይ መደናገርን የሚፈጥሩ ሌሎች ግለሰቦችም ተለይተው የታወቁ እና በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትል ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ፖሊስ ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.