Fana: At a Speed of Life!

ለውጭ ገበያ ከቀረበ የአበባ ምርት ከ184 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የአበባ ምርት ከ184 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አብደላ ነጋሽ÷ በተለይም በአበባ ልማት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዘርፉ ለማግኘት ከታቀደው ጥቅምና የውጭ ምንዛሬ አንፃር ግን አሁንም ዝቅተኛ ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡

በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ወደ ውጭ ለመላክ ከታቀደው 55 ሺህ 852 ቶን የአበባ ምርት ማሳካት የተቻለው 38 ሺህ 949 ቶን ወይም የዕቅዱን ከ69 ነጥብ 57 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተገኘው ገቢም 184 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ቢሆንም ከአምናው ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ገልፀዋል።

የመሠረተ-ልማት አለመሟላት፣ የቅንጅት መጓደልና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በቀጣይ የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል።

በመንግስት በኩል መሟላት አለባቸው ከሚሏቸው መሠረተ ልማቶች አንጻር የውሃ አቀርቦት እና የኃይል መቆራረጥ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአበባ ልማት ላይ በአንዳንዶች ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩ እንቅፋት መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብደላ፤ በግልጽ ማስረዳትና ማሳወቅ እንዲሁም ቅንጅታዊ ሥራዎችን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

በዘርፉ ልማት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች በዓለም ላይ የተፈቀዱና ሥራ ላይ የሚውሉ በመሆናቸው ለሰውም ይሁን ለእንስሳት ጉዳት የሌላቸውና ከአካባቢ ብክለትም ነፃ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለአበባ ልማት የሚውል የመሬት አቅርቦት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለሊዝ አልሚዎች የውል ማቋረጥና ተያያዥ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።

በዘርፉ በስፋት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው አልሚዎች ተጨማሪ መሬት የሚያገኙበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.