Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኦሞ ዞን ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኦሞ ዞን ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጋዲ በርቂ እንደገለጹት፤ የኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ B3-65858 በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ተደብቀው ሲጓጓዙ በነበረበት ወቅት ነው።

ተሽከርካሪው በደቡብ ኦሞ ዞን ከዳሰነች ወረዳ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ እንደነበረም አመልክተዋል።

በወረዳው በቱርሚ እና በዲመካ ከተማ መካከል በሚገኝ ጫካ ውስጥ የሰሌዳ ቁጥሩን ለመቀየር ተሽከርካሪው ቆሞ በነበረበት ወቅት የኮንትሮባንድ እቃዎቹ መያዛቸውን ተናግረዋል።

በተሽከርካሪው ቀደም ሲል ተለጥፎ የነበረውን የአዲስ አበባ ሰሌዳ ቁጥር በደቡብ ክልል ሰሌዳ ቁጥር ለመቀየር ሙከራ መደረጉን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ጋዲ፣ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ትናንት ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ በፖሊስ ሊያዝ ችሏል ብለዋል።

በኮንትሮባንድ ሲጓጓዙ የተያዙት ንብረቶች 7 ሺህ 288 የሞባይል ስልኮች እና 3 ሺህ 140 የሞባይል ባትሪዎች መሆናቸው እንደታወቀም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ለኮንትሮባንድ እቃዎቹ መያዝ የህብረተሰቡና የፖሊስ ቅንጅት ፋይዳ የጎላ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ የተሽከርካሪው ረዳት ለጊዜው መሰወሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ባደረገው አሽከርካሪ ላይ የምርመራ ሥራ መጀመሩንም ጨምረው ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.