ለአማራ ክልል 25 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የደህንነት ካሜራዎች ድጋፍ ተደረጉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለአማራ ክልል 25 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር) በአማራ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተሞች መሠረተልማት ቢሮ ሃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) አስረክበዋል፡፡
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር)÷ተቋሙ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መስክ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ተቋሙ ከተሞችን ስማርት ሲቲ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ጠቁመው÷ይህን ተግባር ወደ አማራ ክልል በማስፋት ከተሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷የተበረከቱት ካሜራዎች በአማራ ክልል የከተሞችን ደህንነት ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ አንስተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለዘርፉ ባለሞያዎች ስልጠናዎችን በመስጠትና የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ ሚናውን እንደሚያጠናክር መገለጹንም የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡