በባንኩ የዲጂታል አገልግሎቶች ከ10 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስምንት ወራት በዲጂታል አገልግሎቶች ከ10 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ማካሄዱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት÷ በተጠቀሰው ጊዜ በባንኩ ዲጂታል አገልግሎቶች በተከናወኑ ከ800 ሚሊየን በላይ ግብይቶች ከ10 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተፈጽሟል፡፡
ይህም ከአጠቃላይ የገንዘብ ዝውውሩ 73 በመቶ መሆኑን ጠቁመው÷32 ሚሊየን የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች በባንኩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በየቀኑም 4 ሚሊየን ደንበኞች በዲጂታል አገልግሎት እንደሚስተናገዱ መጥቀሳቸውን የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የባንኩን ዲጂታል አገልግሎቶች ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ስርዓት መዘርጋቱንም አረጋግጠዋል፡፡