Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልልን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት በሚደረገው ጥረት ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ቴንኩዋይ ጆክ ጠየቁ።

በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

አቶ ቴንኩዋይ ፥ በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት ለመቀየር በሚደረገው ጥረት የባለሃብቶች ተሳትፎና ትብብር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋዎች ቢኖሩም በተፈለገው ደረጃ ባለመልማቱ ህዝቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ተናግረዋል።

ባለሃብቶች በክልሉ ባሉት የግብርና፣ የማዕድን፣ የኢንዱስትሪና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በመሰማራት ራሳቸውን ብሎም አካባቢውን ለመጥቀም ጠንክረው እንዲሰሩም ነው የጠየቁት።

የክልሉ መንግስት በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ወደ ክልሉ ለሚመጡ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ(ዶ/ር) እንደተናገሩት ፥ የክልሉ መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

መድረኩ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማጠናከርና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኡሌሮ ኦፒዮ(ኢ/ር) አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.