ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ዳያስፖራው በጤና ልማት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ዕድል ፈጥሯል- አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘ጽዱ ኢትዮጵያ’ ንቅናቄ ዳያስፖራው በህብረተሰብ ጤና ልማት ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችለውን ዕድል የፈጠረ አጋጣሚ ነው ሲሉ በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የህግ ባለሙያው አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) ገለጹ።
አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገውን ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባርና ንቅናቄ በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
መጸዳጃ ቤትን ጨምሮ የሚታዩ የሳኒቴሽን አገልግሎት ችግሮች በህብረተሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህንን የህብረተሰብ የጤና ችግር ለመፍታት በስፋት መሰራት እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በዚህ ረገድ ለሀገራቸው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሳኒቴሽን ችግር የጤና ቀውስ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሳኒቴሽን ችግርን መፍታት አጠቃላይ የጤና ችግርን መፍታት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ለጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አስተዋጽኦ በማድረግ አጠቃላይ የጤና ልማት ስራዎችን በመደገፍ ዳያስፖራው የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በርከት ያሉ የመጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ዜጎች በንግድ ባንክ አካውንት 1000623230248 እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ ዶላር አካውንት 0101211300016 “ጽዱ ኢትዮጵያ” ማበርከት ይችላሉ።