Fana: At a Speed of Life!

የሸዋል ዒድ በዓል የህዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት እያጠናከረ ይገኛል- አቶ ኦርዲን በድሪ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ቅርስ የሆነው የሸዋል ዒድ በዓል የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡

የሸዋል ዒድ በዓል በአዲስ አበባ በተለያዩ ኩነቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

በዓሉ አብሮነት እንዲጠናከርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል።

ለዚህም ከክልሉ ነዋሪ ባለፈ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች በመሰባሰብ የሚያከብሩት በዓል ነው ብለዋል።

የሸዋል ዒድ በዓል አዲስ አበባ ላይ መከበሩም የህዝቦች ትስስርና ኢትዮጵያዊ አብሮነት እንዲጠናከር እንዲሁም እንደሀገር የወል ትርክት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለታቸውም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የጁገልና የሸዋል ዒድን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶችን ማልማትና ጥቅም ላይ ማዋል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ የክልሉ መንግስትም በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን በማልማት ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም በክልሉ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በቀጣይ የሀረር ከተማ ህዝብን የሰላም፣ የአብሮነትና የእንግዳ ተቀባይነት እሴት በማጠናከር የቱሪዝም ዘርፉን ለማጎልበት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.