Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መስተዳድር ም/ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው በመጀመሪያ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አስመልክቶ የቀረበውን ሪፖርት ተመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ ባደረገው ግምገማ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ በርካታ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በጠንካራ ጎን ገምግሟል።

ከለውጥ በኃላ ብዙ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች መመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን÷መሬት ወስደው ወደ ስራ ያልገቡት ላይ የተጀመረ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባላቱ ጠይቀዋል።

የክልሉን እምቅ አቅም ያገናዘበ የኢንቨስትመንት ክላስተር ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅም ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ወደ ስራ የገቡ ኢንቨስትመንቶች የፈጠሩት የስራ ዕድልም ከፍ ባለ ቁጥር እንዲጨምር እንዲሁም የሚያከናወኑት ኮርፖሬት ማህበራዊ ኃላፊነት ላይ ትኩረት እንዲደረግም አቅጣጫ ተቀምጧል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በሁለተኛነት የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማሻሻል፣ለማደራጀትና ስልጣንና ተግባራት ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅን ተመልክቷል።

አሁን ያለው መንግስታዊ አወቃቀር ለአዳጊ ተለዋጭ ሁኔታዎች ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት፣ የተልዕኮ ትስስርና እርስ በርስ ተናቦና ተቀናጅቶ የመስራት ፋይዳ ታሳቢ አድርጎ እንደገና በመቃኘትና በመከለስ አንጻራዊ ማስተካከያ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ ወደ ም/ቤቱ መርቶታል።

በሶስተኛ ደረጃ የተለያዩ ተቋማትን ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር የወጣ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ፣የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደርና ኤጄንሲን ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብ፣ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በአራተኛ አጀንዳነት የተመለከተው ክልሉ የራሱ ሚዲያ እንዲኖረው ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀውን“የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ” ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ነው።

የክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ክልላዊ የሚዲያ ኔትወርክ መመስረት ረቂቅ አዋጅ ሲሆን÷ አሁን ባለው የቴክኖሎጂ ዘመን ትክክለኛና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ከሚዲያ ተወዳዳሪነትና ከመረጃ ተደራሽነት አኳያ ለክልሉ ያለው አበርክቶ የላቀ መሆኑ ተገንዝቧል።

ስለሆነም የሚዲያ ኔትወርክ ተቋቁሞ ስራ ላይ እንዲውል የቀረበውን የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ወደ ክልሉ ምክር ቤት መምራቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.