Fana: At a Speed of Life!

የውሃ ማጣሪያ ማሽን ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢቲዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና አፒሞሶ ከተሰኘ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያ ጋር የውሃ ማጣሪያ ማሽን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት፣ ለመገጣጠምና ለማምረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ እና የአፒሞሶ ካምፓኒ ተወካይ ሚላን ተፈራርመዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ ከቼክ ሪፐብሊክ መንግስት ጋር በውሃ ሃብት ልማት ላይ በተለይ በከርሰምድር ውሃ ጥናት በትብብር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ወደፊት ከካምፓኒው ለሚያስገባቸው፤ ለሚያሰራጫቸው፣ ለሚገጣጥማቸውና ለሚያመርታቸው የውሃ ማጣሪያ ማሽኖች በሀገሪቱ በተቀመጡ መስፈርቶችና ደንቦችን መሰረት በማድረግ የቁጥጥርና ድጋፍ ስራ ለመስራት መስማማቱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮኢንጂነርንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በበኩላቸው÷ ስምምነቱ በዘርፉ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡

ማሽነሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት፣ ለማከፋፈል፣ ለመገጣጠም ሆነ በማምረት ወደ ገበያ ለመግባት ተቋማቸው ዝግጁ እንደሆነ መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.