Fana: At a Speed of Life!

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ እና በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ከ80 በላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረኮች የተገኙ ሀሳቦችን መሰረት በማድረግ በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን የተዘጋጀው ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ም/ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የተመላከቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመፈጸም ረገድ የትግበራ ምዕራፉ መቼና እንዴት ተጀምሮ ተፈጻሚነቱ የሚያበቃበትን ሁኔታ ለማመላከት የፍኖተ ካርታ ወይም ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ መሰረትም ይህንን በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ በተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች የተፈጠሩ ቁስሎችን በተለያዩ የሽግግር ፍትህ ስልቶች አማካኝነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት መስጠት የሚያስችል ማስፈጸሚያ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፍኖተ ካርታው ዘላቂ ሰላምን፣ የህግ የበላይነትን፣ ፍትህን እና የሰብዓዊ መብትን ለማረጋገጥ የተቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችም ተጠቅሷል፡፡

የፍኖተ ካርታው ዝግጅት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ከሲቪል ማህበረሰብ ብሔራዊ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በያዘ ቡድን እየተከናወነ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ፍኖተ ካርታው የፖሊሲ ትግበራ ምዕራፉ የሚያልፍባቸውን ሒደቶች በዝርዝር ከማመላከት በተጨማሪ በፖሊሲው ትግበራ የባለድርሻ አካላትን ሚና፣ የመፈጸሚያ የጊዜ ወሰንን እና ሥራው የሚጠይቀውን የበጀት መጠን ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፍኖተ ካርታው ዝግጅት በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ የሚገባ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.