Fana: At a Speed of Life!

የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ተጠይቋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ም/ቤቶች ፌደሬሽን የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ሌንጮ በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ገልጸው÷ ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱና ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የሳዑዲ ባለሃብቶች በግብርና፣ በማዕድን፣ በሪል ስቴት፣ በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች ቢሳተፉ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች በኤምባሲው በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ የንግድ ም/ቤቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ሐሠን አልሑወይዚ በበኩላቸው ÷በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመረዳት ከ50 አስከ 60 የሚሆኑና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለሃብቶችን ያቀፈ የልዑካን ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡

ጉብኝቱ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ በማመቻቸት ኤምባሲው የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግላቸውም መጠየቃቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ለማደረግ ላቀደው የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ሚሲዮኑ አስፈላጊውን ሁሉ በማመቻቸት ጉብኝቱ የተሳካ እንዲሆን የሚያስችል ድጋፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.