Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2017 ዓ/ም በጀት ሰሚ መድረክ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2017 ዓ/ም በጀት ሰሚ መድረክ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካለኝ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡

የበጀት ሰሚ መድረኩን የመሩት አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት ÷ የ2017 ዓ/ም የበጀት ዝግጅቱ ዓላማ የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው በ2016 እስከ 2ዐ18 ዓ/ም የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ማስፈጸምና የመንግስትን ፈጣን፣ ፍትሃዊና ዘላቂ የዕድገት ፖሊሲን ማረጋገጥ ነው፡፡

በዛሬው የመጀመሪያ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2017 ዓ/ም በጀት ሰሚ መድረክ የስራና ክህሎት፣ የቱሪዝም፣ የባህልና ስፖርት እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስትሮችና የተጠሪ ባለበጀት መስሪያ ቤቶቻቸው በጀት ተገምግሟል፡፡

በበጀት ግምገማ መድረኩ ለባለበጀት መስሪያ ቤቶቹ በገንዘብ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ሙያዊ አስተያየት የተሰጣቸው ሲሆን ፥ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በተሰጣቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት የ2017 በጀታቸውን አስተካክለው እንዲያቀርቡ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡

እስከ ግንቦት 9/ 2016 ዓ/ም በሚዘልቀው በዚህ የበጀት ሰሚ መድረክ ከ160 በላይ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2017 ዓ/ም በጀታቸውን አቅርበው እንደሚያስገመግሙ መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.