Fana: At a Speed of Life!

ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት የግሉ ዘርፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት የግል ኩባንያው ዘርፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ተመላከተ፡፡

የኩባንያዎች ዝግጁነት ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በሚል መሪ ሐሳብ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያዘጋጀው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለኢትዮጵያ የንግድ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው እና ዓለም አቀፍ የንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣትም አስቻይ መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የመድረኩ ዓላማም ሊጠቅሙ የሚችሉ እና መንግስት ሊያዳምጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ሕዝብ መገበያያ ይሆናል የተባለው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የ3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ዓመታዊ ምርት ድርሻ እንዳለው በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ 47 ሀገራት ስምምነቱን ለመተግበር የሀገራቸው ሕግ አድርገው እንዳጸደቁትም ተገልጿል።

ዛሬው ውይይትም ኩባንያዎች ይህን ስምምነት በመተግበር ሂደት ውስጥ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።

በመድረኩም ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት የግል ኩባንያው ዘርፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ እንደሚጠበቅበት እና የቁጥጥር እና ክትትል ሥራውም በመንግሥት እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.