Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሚገኙ የመስህብ ሥፍራዎችን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንደገለጹት ፥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ሥፍራዎችን ከ112 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ጎብኝተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 5ሺህ 428 የሚሆኑት የውጭ ሀገር ቱሪስቶች መሆናቸውንና ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ66 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት፣ የማበልፀግና የማስተዋወቅ ሥራ በሰፊው መሰራቱ ለጎብኚዎች ቁጥር መጨመር አንዱ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘጠኝ ወራቱ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ሥፍራዎችን ከጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።

እንደ አቶ ተወለዳ ገለጻ ፥ በቱሪስቶች ከተጎበኙት ቅርሶች መካከል የጁገል ግንብ ዓለም አቀፍ ቅርስ እና በውስጡ የሚገኙ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም አምስቱ የጁገል ግንብ መግቢያ በሮች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቦ መኖሪያ ቤት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ ሙዚየሞች፣ አድባራት፣ የጅብ ምገባ ትርኢትና ሌሎችም ቅርሶች በቱሪስቶች መጎብኘታቸውን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.