Fana: At a Speed of Life!

የከርሰ ምድር ውሃ ሃብቶቻችን በጋራ የመልማታችን ማሳያ ሊሆኑ ይገባል – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከርሰ ምድር ውሃ ሃብቶቻችን በጋራ የመልማታችን ማሳያ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ አባል ሀገራት የድንበር ተሻጋሪ ከርሰ ምድር ውሃ ሀብቶቻቸውን በጋራ አልምተው መጠቀም በሚችሉበት የከርሰ ምድር ውሃ ተደራሽነት አጠቃቀም ፕሮግራም ዙሪያ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ወረዳ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡

በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ፥ የኢጋድ አባል ሀገራት ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋና ሀይማኖት እንዳላቸው ሁሉ እምቅ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ባለቤቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህንን ሀብታቸውን በጋራ አልምተው በመጠቀም የዜጎቻቸውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ሊፈቱ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንም ሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብቶቻችን የፉክክር መነሻ ሳይሆን በጋራ የመልማታችን ማሳያ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጁቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ የውሃ ሚኒስትሮች በበኩላቸው ፥ የድንበር አካባቢ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትን በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የውሃ ሚኒስትሮቹ በነገው ዕለት የቶጎ ውጫሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አተገባበርን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጎህ ንጉሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.