ለ30 ዓመታት ፊቱ ከታፋው ጋር ተጣብቆ የቆየው ግለሰብ በተደረገለት ቀዶ ጥገና ቀጥ ብሎ መቆም ችሏል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሶስት አስርት ዓመታት ፊቱ ከታፋው ጋር ተጣብቆ የቆየው ግለሰብ በተደረገለት የተሳካ ቀዶ ጥገና ህክምና ቀጥ ብሎ መቆም መቻሉ ብዙዎችን አስደስቷል።
የ46 ዓመቱ ሊ ሁዌ ከ18 ዓመቱ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት ፊቱን ከታፋው ጋር በማጣበቅ ያሳለፈው አንኪይሎሲንግ ስፖንዳይሊቲስ በተባለ ያልተለመደ በሽታ በመጠቃቱ ነው።
ሊ ሁዌ በደቡብ ቻይና ጓንግዶንግ ግዛት በሚገኘው ሼይንዚን ዩኒቨርስቲ አጠቃላይ ሆስፒታል በተደረገላቸው የተሳካ ቀዶ ጥገና ህክምናም እንደገና ቀጥ ብሎ መቆም ችሏል ፡፡
ሆስፒታሉ የተደረገው የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት የኤቨረስት ተራራን የመውጣት ያክል ከባድ እንደነበር አስታውቋል።
በሆስፒታሉ መሰል በሽታ የተጠቁ ሰዎችን የሚረዱት በአከርካሪ ቀዶ ጥገና እና የአጥንት ህክምና ሀላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ታኦ ሁዬሬን በሁኔታው መገረማቸቸውን ይናገራሉ።
የቀዶ ጥገና ባለሙያው ምንም እንኳ መሰል በሽታዎች ሲያክሙ ቢቆዩም እንዲህ ዓይነቱን ከባድ በሽታ ግን በጭራሽ እንዳላጋጠማቸው ነው የተናገሩት፡፡
ቀዶ ጥገናውም በአራት ደረጃዎች የአከርካሪ አጥንቱን በርካታ ክፍሎች ላይ በመስበር የተከናወነው ሲሆን ፥
ውጤቱ በሚገርም ሁኔታ የተሳካ መሆኑም ተመላክቷል።
ሊ ሁዌ ከቀዶ ጥገናው በፊት ለመብላትም ሆን ለመጠጣት ይቸገር የነበረ ሲሆን፥ አሁን ግን ቴኒስ መጫወት እና መሰል ድርጊቶችን ማከናወን ባይችልም መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡-ኦዲቲ ሴንተራል