Fana: At a Speed of Life!

ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ችግሮችን ለመፍታት አመራሩ በብቃት መስራት አለበት – የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት አመራሩ በብቃት መስራት እንዳለበት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
 
የሰላም ሚኒስቴር ከክልል እስከ ወረዳ ለተወጣጡ አመራሮች በአዲስ አበባ ከተማ በሁለተኛ ዙር ለሦስት ቀናት ያካሄደው ሃገራዊ የምክክርና የተሳትፎ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።
 
በአገራዊ የምክክርና የተሳትፎ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ባደረጉት ንግግር መድረኩ ግብዓት የተወሰደበት መሆኑን ተናግረዋል።
 
በውይይት መድረኩ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ውጤታማ ውይይት እንደተደረገ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ “ይህም የአመራሩን አቅም ለመገንባት፣ ክህሎትና ብቃቱን ለማሳደግ አስተዋጽኦዖ የጎላ ነው” ብለዋል።
 
በዴሞክራሲ የሽግግር ሂደት የተለያዩ አገሮች ዛሬ ላይ የደረሱት በርካታ ፈተናዎችን አልፈው መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያም የዴሞክራሲ ሽግግር እውን እንዲሆን የሁሉም የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
 
በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ለሰላም ግንባታ ተቋም ከማቋቋም ባለፈ ካለፈው ትምህርት ተወስዶ ዛሬን እና ነገን መቀየር የሚችል የአስተሳሰብ ለውጥ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ አክለዋል።
 
ወይዘሮ ሙፈሪያት እንዳሉት፤ በአገራዊ የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ አገር በቀል የእርቅ፣ የድርድር እና የሽምግልና ባህል ከተረሳበት ከፍ እንዲል በማድረግና አሟጦ በመጠቀም ለሰላም መዳበር እንደ ዋነኛ ግብ እየተወሰደ ነው።
 
የሰላም ጉዳይ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም ሚናውን ለመወጣት ተሳትፎውን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
 
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት አመራሩ በብቃት መስራት እንዳለበትም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ሚኒስትሯ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በትናንትናው ዕለት በንፁሀን ዜጎች ላይ በተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፣ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.