Fana: At a Speed of Life!

በከሃዲና ፅንፈኛ ቡድን ሴራ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን አይናድም- መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ፡፡
 
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል:-
 
በከሃዲና ፅንፈኛ ቡድን ሴራ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን አይናድም!
 
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በሃገራችን እየተካሄደ ባለው ሁለንተናዊ ለውጥ የትግራይ ህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን በእጅጉ የሚጎዱ ተግባራትን ሲያካሂድ የቆየው በህወሃት ውስጥ መሽጎ የሚገኝ የማይለወጥና ቆሞ ቀር ቡድን ራሱን ከለውጡ ጋር በማላመድ የሃገራችንን ትንሳኤ ለማረጋገጥ በሚደረገው የለውጡ ጉዞ ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
 
ይሁንና ይህ አጥፊና ህገ ወጥ ቡድን ከጅምሩ ጀምሮ ለውጡ እንዲደናቀፍ የተለያዩ ሴራዎችን በመሸረብ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፤አካል እንዲጎድል፤ንብረት እንዲወድምና በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
 
ይባስ ብሎ የሰራዊታችንን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲገድብ የቆየው አሸባሪ ቡድን የሃገር ምልክትና የኢትዮጵያ ህዝቦች ተምሳሌት በሆነው በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት ከፍቷል፡፡
 
የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን የሃገርን ሉአላዊ ክብር ለማስጠበቅ በተሰማራበት የትግራይ ክልል በጽንፈኛና ከሃዲ ቡድኖች የተሰነዘረበትን ጥቃት በተደራጀ መልኩ በታላቅ ሃገራዊ ፍቅርና የጀግንነት ስሜት እየመከተ ይገኛል፡፡
 
ጽንፈኛውና ከሃዲው ቡድን አነስተኛ የሰው ሃይል ባለበት የሰራዊታችን ካምፖች ድንገተኝነትን ተጠቅሞ ጥቃት ቢፈፅምም ጀግናው ሰራዊታችን ግን ወትሮም ዋጋ ከፍሎ ሃገርን ማዳን ልምዱ ነውና የተቃጣበትን ጥቃት ለመመከት ፅንፈኞችን በመፋለም ላይ ነው፡፡
 
በሃገር ንብረት ዘረፋ፤በግድያ ፤በአካል ማጉደልና በሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚታወቀው ከሃዲውና ጽንፈኛው ቡድን በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሰራዊታችንንና የሌሎች ሃገራትን ዪኒፎርም አስቀድሞ አመሳስሎ በማምረትና የራሱን ሃይል በማልበስ ገድለናል፤ማርከናል የሚል የተለመደ ማደናገሪያውን የክልሉን ሚዲያ ተጠቅሞ በመንዛት ላይ ይገኛል፡፡
 
እውነታው ግን ጀግናው ሰራዊታችን በታላቅ ጀግንነት፤በፍፁም የሃገር ፍቅር ስሜትና በአንድነት መንፈስ የፅንፈኛውና የከሃዲውን ጥቃት መመከቱ ነው፡፡
 
እንደሚታወቀው እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትፍረስ የሚለው የስልጣን ጥመኛው ቡድን ያሰባሰበው የልዩ ሃይልና ሚሊሻ በአንዳንድ አካባቢዎች የመዋጋት ፍላጎት የሌለው ሲሆን መንግስት ዋስትና እንዲሰጠውም ይፈልጋል፡፡
 
ተገዳችሁና ሳትፈልጉ ወደ ጦርነት የገባችሁ የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል አባላት!
 
በሰላማዊ መንገድ ወደ አጎራባች ክልሎችና በአቅራቢያችሁ ወዳለው የመከላከያ ሰራዊት ከገባችሁ መንግስት ሙሉና አስተማማኝ ዋስትና እንደሚሰጣችሁ ያረጋግጥላችyል፡፡
 
ውድ የትግራይ ህዝቦች!
 
ሰላማችሁን ለማስጠበቅ ከሃያ አመታት በላይ ከጎናችሁ ተሰልፎ የተዋደቀውን የሃገር መከላከያ ሰራዊት፤ችግራችሁን እየተካፈለና ልማታችሁን እየደገፈ አብሯችሁ በመልካም ወንድማማችነት የኖረውን ይህንን ጀግና ሰራዊት፤መውጋት ታሪክ ይቅር የማይለው የትግራይን ህዝብ የማይመጥን ከመሆኑ ባሻገር በዓለም ታሪክ አንድ መደበኛ ጦር በደባና በአሻጥር በገዛ ወገኑ ተወግቶ የማያውቅ መሆኑን ተረድታችሁ በዚህ አሳፋሪ ድርጊት ባለመሳተፍና ከሰራዊታችን ጎን በመሰለፍ የተለመደ ጀግንነትና ቁርጠኝነታችሁን እንድታረጋግጡ ጥሪ እናቀርብላችለን፡፡
 
ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች!
 
የሃገርን ሉአላዊ ክብር ለማስጠበቅ የቆመን ሰራዊት፤ሃገር እንጂ ብሄር የሌለውን ሰራዊት ፤የኢትዮጵያ ህዝቦች ትክክለኛ ተምሳሌት የሆነን ህብረ ብሄራዊ ሰራዊት፤ከሃገር አልፎ በአለም አቀፍ ሰላም ላይ ዝናና አክብሮትን ያተረፈን ሰራዊት ማጥቃት ሃገርን ተኩሶ እንደ መግደልና የኢትዮጵያውያንን ክብር እንደ መንካት ይቆጠራል፡፡
 
የሃገር መከላከያ ሰራዊት ትናንት ከላብ ጠብታ እስከ ህይወት መስዋእትነት በመክፈል ዛሬም በገንዘቡና በጉልበቱ መላ ህዝቡን እየደገፈ የመጣ ምስጋና እንጂ ጥቃት የማይገባው የህዝብ ልጅ መሆኑን አስታውሳችሁ ይህንን ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እንድታወግዙትና የሃገራችንን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለማስከበርና አጠናክሮ ለማስቀጠል በምንወስደው እርምጃ ከጎናችን እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
 
ድል ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችን
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት
ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.