ኢትዮጵያና እስራኤል በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ተባብረው ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና እስራኤል በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል ።
የእስራኤል ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኮሚሽነር ደምላሽ ገብረ ሚካኤል ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል ።
በውይይታቸውም ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት፣ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በአቅም ግንባታ ዘርፍ ይበልጥ ተባብረው ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል ።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ኮሚሽነር ደምላሽ ገብረሚካኤል በውይይቱ ወቅት ÷ ኢትዮጵያና እስራኤል በመረጃና ደህንነት ዘርፉ ተባብረው ቢሰሩ በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው ሰላምና መራጋጋት በማጠናከር በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ ብለዋል ።
የእስራኤል ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና ያላትና ተሰሚ በመሆኗ ምክንያት እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር በመረጃና ደህንነት ዘርፉ ያላትን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያ በመረጃ ዘርፍ የጀመረችውን ለውጥ እስራኤል እንደምትደግፍም ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያና እስራኤልም በመረጃና ደህንነት ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የደረሱትን ስምምነት በቅርቡ ወደ ተግባር ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የላከው መረጃ አመልክቷል ።