የአውሮፓ ህብረት በቤላሩሱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ላይ ማዕቀብ ጣለ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በቤላሩሱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ላይ ማዕቀብ ጣለ፡፡
ህብረቱ በሃገሪቱ ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው አለመረጋጋት መንግስት በንጹሃን ላይ ለወሰደው የሃይል እርምጃ ነው ማዕቀቡን የጣለው ተብሏል፡፡
ከእርሳቸው ባለፈም ልጃቸው ቪክቶር ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በህብረቱ የጥቁር መዝገብ የሰፈሩ ባለስልጣናት ቁጥርም 59 ደርሷል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም የቤላሩስ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አጎር ሰርጌንኮን ጨምሮ 15 ሰዎች ላይ ህብረቱ አዲስ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል፡፡
ባለፈው ነሃሴ ወር በተካሄደው ምርጫ ፕሬዚዳንት ሉካሼንኮ አሸንፌያለሁ ቢሉም፥ ውጤቱ በህብረቱም ሆነ በታዛቢዎች ተቀባይነት አላገኘም፡፡
ምርጫውን ለመታዘብ የተዋቀረው ኮሚቴም ከምርጫው ውጤት ማግስት የሉካሼንኮ አስተዳደር ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
አሁን የተጣለው ማዕቀብ እና እገዳም የግለሰቦቹን ሃብትና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ማገድን ጨምሮ በተጠቀሱት ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እና የእንቅስቃሴ ገደብን የሚጥል ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም በህብረቱ አባል የሆኑ ሃገራት ግለሰቦች እና ተቋሞቻቸው በዝርዝሩ ለተካተቱት ባለስልጣናት ገንዘብ እንዳያበድሩም ይከለክላል፡፡
የሉካሼንኮ አስተዳደር ከምዕራባውያን ጫና ቢበረታበትም ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ድጋፍ አግኝቷል፡፡
ምንጭ፦ ቢቢሲ