Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በአምስት ወራት ውስጥ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት አመቱ አምስት ወራት ውስጥ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለፀ።

የቢሮው ሀላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን እንደገለፁት፥ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ነው የተጠቀሰውን ገቢ የሰበሰበው።

ከአምና ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የሰበሰበው ገቢ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ሃላፊዋ ተናግረዋል።

በበጀት አመቱ መጀመሪያ የግብር አሰባሠብ የንቅናቄ ስራ መሠራቱ እና የክትትልና የድጋፍ ስራው መሻሻል ደግሞ ለገቢው እድገት ምክንያቶች ናቸው ብለዋል ወይዘሮ ብዙአየሁ።

በሌላ በኩል የሠው ሀይል መሟላት፣ የሞያተኛውና የአመራሩ የስራ ተነሳሽነት እና በዚህ አመት በሃገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የግብር አሠባሠብ መመሪያ መኖሩ ለጭማሬው አስተዋፅኦ ነበርው ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ ከዕቅዱ አንፃር ብዙ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዚህም የግብር ከፋዮ ደርሠኝ የመስጠትና የማህበረሠቡ ደርሠኝ የመቀበል ልምድ ውስንነት፣ የታክስ ማጭበርበር፣ የተወሠኑ አመራሮችና ሞያተኞች የስነምግባር ችግር እና የግብር ከፉዮችን መረጃ በአግባቡ አለማያዝ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ ተነስቷል።

ችግሮቹን ለመፍታት የግብር ከፋዮችን መረጃ  በአግባቡ መያዝ የሚስችል ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን እንዲሁም የስነምግባር ችግር ያለባቸው አመራሮች እና ሙያተኞች ላይም እርማጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡

ቢሮው በበጀት አመቱ 14 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.