Fana: At a Speed of Life!

የሀረሪ ክልል እና የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ሀላፊዎች በሀረሪ ክልል ከሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል እና ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ሀላፊዎች በሀረሪ ክልል ከሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር ተወያዩ።

የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በውይይት መድረኩ÷ ህወሓት የትግራይ ህዝብን አይወክልም ከዚህ ጋር በተያያዘ ያሉ የአመለካከት ክፍተቶች ሊቀረፉ ይገባል ለዚህም ፓርቲው በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ ከጁንታው ህወሓት ጋር በመገናኘት በተግባር ችግር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጥፋት ሀይሎችን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከክልሉ መንግሥት እና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት ቀሪ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሀብቱ በበኩላቸው ÷ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ በተለይም የትግራይ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ እንቅስቃሴ ተደርጓል በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አውስተዋል።

የተካሄደው ህግን የማስከበር ተግባር ውጤታማ የሆነውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የትግራይ ህዝብ ከጎኑ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በክልሉ ከሚገኙ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እና ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት ሰላምን የማስፈን እና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ እየተደረጉ ባሉ ተግባራት ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የትግራይ ተወላጅ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተዋልዶና ተዋዶ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ ለሀገሪቱ ሰላም እንደከዚህ ቀደሙ በግንባር ቀደምትነት እንደሚሰለፉ አረጋግጠዋል።

ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ፥ ከዚህ ጋር ተያይዞም አልፎ አልፎ የሚታዩ የአመለካከት ክፍተቶች ሊታረሙ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት የሚወገዝና መሆንም ያልነበረበት ተግባር መሆኑን በማንሳትም ለሀገሪቱ ሰላም እያከናወኑ ያለውን ተግባር እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የድህነት መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም ይህም ህወሓት የትግራይን ህዝብ እንዳልጠቀመ ማሳያ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የትግራይ ህዝብና ተወላጅ እንደከዚህ ቀደሙ የሀገር መከታነቱን ማሳየት እንደሚገባ መናገራቸውን ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
579
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.